በእስራኤል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ልዩ መልዕከተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሻሮን ባር-ሊ ጋር ውይይት አካሄደዋል፡፡

በውይይታቸው ወቅት ክቡር አምባሳደር ኢትዮጵያ እና እስራኤል ረጅም ዘመን ያስቆጠረ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው እና በቆይታቸው ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከህ.ወ.ሃ.ት ጋር በነበረ ግጭት ምክንያት አገራችን አስቸጋሪ ወቅት ማሳለፏን ገልጸው ባለፈው ህዳር ወር ዘላቂ ሰላም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ መፈረሙን አክለው ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን እና ከፌዴራል መንግስት ጋር መልካም መተማመን መፈጠሩን አሳውቀዋል፡፡ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለከተም ግብጽ ጉዳዩን ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ እየጣረች መሆኑን ኢትዮጵያ ደግሞ ጉዳዩን የአፍሪካ በመሆኑ በአፍሪካ ማዕቀፍ መታየት እንደሚገባ የሚል አቋም እንደምታራምድ አሳውቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሁለትዮሽ ትብብሩን የበለጠ ስለማጠናከር እና በተለያዩ መስኮች ስለሚሰፋበት ሁኔታም ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሻሮን ባር-ሊ በበኩላቸው ኢትዮጵያ እና እስራኤል አሁን ያላቸው ግንኙነት በኢኮኖሚም ዘርፍ የማስፋት ሰፊ እድል እንዳላቸው፣ ይህንንም በኢንቨስትመንት ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ እህትማማች አገሮች በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ይበልጥ መተባበር እንደሚገባቸው ጠቅሰው እስራኤል በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የነበራትን የታዛቢነት መቀመጫ መልሳ እንድታገኝ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ባላት ተጽዕኖ እና ተሰሚነት ድጋፍ እንድታደርግ አጽንኦት ሰጥተው ጠይቀዋል፡፡በውይይቱ የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የስራ ዘርፍ ኃላፊ አሚት ጊል ባያዝ እና የኢትዮጵያ ዴስክ ኦፊሰር ቶመር ባር-ላቪ ተሳትፈዋል፡፡

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram