127ኛው የዓድዋ የድል በዓል በእስራኤል ኢትዮጵያ ኢምባሲ “ዓድዋ፤ አንድነት፣ ጀግንነትና ጽናት!” በሚለው መሪ ቃል የካቲት 27 ቀን 2015 ዓ.ም. ኢትዮጵያውያን፣ ቤተ-እስራኤላውያን/ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተወካዮችና አስተባባሪዎች እንዲሁም የኢምባሲው ባልደረቦች በተገኙበት ተከብሯል።

በዚህ የኣድዋ ድል መታሰቢያ በዓል አምባሳደር ነጋ ፀጋዬ የሚስዮኑ ተ/ጉዳይ ፈፃሚ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጀግንነት፣ በአንድነት እና በነበራቸው ጽናት የጣሊያንን ወራሪና ቅኝ ገዥ ኃይል ቅስም በመስበር የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበረ መሆኑን፣ ድሉ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያንና የመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት መገለጫ መሆኑን፣ አገራችን ከጣሊያን ወራሪ ጋር ወደ ጦርነት የገባችበትን መንስኤ፣ የኢትዮጵያውያንን የዲፕሎማሲ ትግል፣ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች ለነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ የድሉን ትሩፋቶችና ፋይዳዎች በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ አምባሳደር ነጋ በማጠቃለያቸውም የዘመናችን አድዋ የሆነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እና መሰል ትልልቅ ሃገራዊ ፕሮጀክቶቻችንን በመደገፍ እያደረጋችሁት ያለውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ በመቀጠል የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ገድልና ታሪክ የዓድዋን ድል እንድንደግም በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ ከተገኙት ተሳታፊዎች መካከል በተለያዩ የአለም አገራት ለሚገኙ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች በኢትዮጵያ በተደረገው የእውቅናና ምስጋና ፕሮግራም የተሳተፉና በቅርቡ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የጎበኙ በእስራኤል የኢትዮጵያ ህዳሴ ምክር-ቤት ሰብሳቢ አቶ ራህሚም አላዛር እና የጥቁር አንበሳ ኢትዮ-እስራኤል ግሎባል ዩኒቲ ማህበር ሰብሳቢ ራብ ያፌት አለሙ የዓድዋ በዓልን እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በሚመለከት ለተሳታፊዎቹ ሰፋ ያለ ገለጻ ሰጥተዋል። በገለጻቸውም ህዳሴ ግድቡ ዳግማዊ ዓድዋና ድህነትን ድል የሚያደርግ መሆኑን፣ ለትውልድ ኩራት መሆኑን እና ግድቡ መላው ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን በአንድነት አሻራቸውን ያኖሩበት መሆኑን አስረድተዋል። ቤተ-እስራኤላውያን በአድዋ ጦርነት በቀጥታ ከመሳተፋቸው ባሻገር በመሳሪያ ማምረትና ለወታደሮች በማቅረብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የቀድሞ ክኔሴት(ፓርላማ) አባል ዶ/ር አብረሃም ንጉሴ አያት ቅድመ-አያቶቻችን በዘመኑ በአንድነት፣ በቆራጥነትና ጽናት የወቅቱን ጠላት ማሳፈር መቻላቸውን፣ የእኛም ትውልድ እንደቀደሙት አባቶቻችን ሁሉ በእስራኤል የምንኖር ኢትዮጵያውያን፣ ቤተ-እስራኤላውያን/ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ልማትና እድገት በሚደረገው እንቅስቃሴ እያደረግን ያለውን ድጋፍና ትብብር አጠናክረን መቀጠል ይገባናል በማለት አሳስበዋል ።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram