በእስራኤል የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና Tal Aviation በጋራ በመሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሥራ እንቅስቃሴ እንዲሁም የአገራችንን ቱሪዝም ሃብቶችን በእስራኤል ለሚገኙ የቱር ኦፕሬተሮች ለማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ ተዘጋጅቷል።

በዚህ መድረክ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ስለአገራችን የቱሪዝም መስህቦች፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከመቸውም ጊዜ በላይ መንግስታችን ለቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰሩ ያሉ በርካታ ተግባራትን በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል። አምባሳደር ተስፋዬ ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን አስታውሰው፤ ሁለቱ ሀገራት ከታሪካዊ ግንኙነታቸው፣ ከመልክዓ ምድር ቅርበታቸው፣ በአገራችን ዘርፈ ብዙ የቱሪዝም መስህቦች መኖራቸው እንደዚሁም በየቀኑ ከሚደረገው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ አንጻር ሲታይ ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ያለውን የቱሪስት ፍሰት መጨመር እንደሚገባ ለቱር ኦፕሬተሮች አስረድተዋል።  አክለውም የኢትዮጵያ መንግስት ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት በአጽንኦት ገልጸዋል።

በዚህ መድረክ ንግግር ያደረጉ በቴል አቪቭ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ቅርንጫፍ እና Tal Aviation የሥራ ኃላፊዎች  የመድረኩ ዓላማ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስኬታማ የሥራ እንቀስቃሴ በማስተዋወቅ ገጽታ ከመገንባት በተጨማሪ ከእስራአል ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገውን የቱሪስት ፍሰትን መጨመር መሆኑን ገልፀው፤ ለዚህም “BACK TO ORIGIN” በሚል ትውልድ ኢትዮጵያዊ የሆኑ እስራኤላውያንን የአገራችንን ቱሪስት መዳረሻዎችን በተሻለ ወጪ መጎብኝት የሚችሉበትን “ፓኬጅ” አስተዋዉቀዋል።

በተጨማሪም “ አ AVRISH” የተባለ አስጎብኝ ድርጅት ኃላፊ በአገራችን በዘርፉ ያለውን ልምድ በሚመለከት ንግግር ባደረጉበት ወቅት፤ ኢትዮጵያ በቱሪዝም በርካታ ዕድሎች ያሏት መሆኑን ለተሳተፊዎች ገልፀዋል። በመድረኩ በአፍሪካ እና በተለያዩ አህጉራት የሚቀሳቀሱ 25 የቱር ኦፕሬተሮች ተሳትፈዋል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram