ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ከእስራኤል ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር (MASHAV) ኃላፊ Ambassador Eynat Shlein ጋር ዛሬ ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም  በመ/ቤታቸው ተገኝተው ውይይት አካሂደዋል።

ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ በኢትዮጵያ እና  እስራኤል መካከል ጠንካራ ታሪካዊ እና  የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መኖሩን ገልጸው MASHAV በአገራችን እያከናወነ ለሚገኘው የልማት እገዛዎች አመስግነዋል፡፡  ኢትዮጵያ ለመልማት በምታደርገው መጠነ ሰፊ ግስጋሴ ውስጥ ማሻቭ እያካሄደ ያለው  የእውቀት እና ክህሎት ሽግግር አስተዋጽኦ እንዳበረከተ የአቮካዶ ፕሮጀክትን  በመጥቀስ በአገራችን በአሁኑ ወቅት የአቮካዶ ምርት ኤክስፖርት ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ አገራችን የልማት፣የአቅም ግንባታ እና የእውቀት ሽግግር በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርትና ሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ባላቸው መስኮች ተጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎት እንዳላት እና እርሳቸውም ለዚሁ ስኬት ከተቋሙ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ አክለው ገልጸዋል፡፡

Ambassador Eynat Shlein በበኩላቸው ስለMASHAV ዓለም አቀፍ የአቅም ግንባታ ስራዎች አብራርተው በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየተሰሩ ካሉት ፕሮጀክቶች በበርካታ ዘርፎች የማስፋት እድል እንዳለ ገልጸዋል፡፡ መንግስታቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላለው ግንኙነት ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጹት ኃላፊዋ ወደፊት MASHAV በሚያዘጋጃቸው የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ኢትዮጵያውያን ሰልጣኞችን ለማካተት እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም MASHAV ያለውን የስልጠና ማዕከላት ጉብኝት ለማዘጋጀት፣ የከፍተኛ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የልምድ ልውውጥ ለማመቻቸት እና ቀጣይ በሚኖሩ ስልጠናዎች በጋራ ለመስራት በመግባባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

 

  

 

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram