በእስራኤል 11ኛውን ዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ ቀንን ምክንያት በማድረግ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም. በቴል-አቪቭ በተዘጋጀው የፎቶ አውደ ርዕይ ላይ ተሳትፎ ተደርጓል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር እና ቤተ-እስራኤላውያን ኩነቱን በማዘጋጀታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡ “ቀድሞ የነበረውን የማያውቅ ወደፊት የሚሄድበትን አያውቅም” ያሉት ክቡር አምባሳደር ቤተ-እስራኤላውያን በኢትዮጵያ የነበራቸውን አኗኗር፣ ባህልና ወደ እስራኤል የመጡበትን ሂደት በሚያንጸባርቅ መልኩ አቆይቶ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፉ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ያለው ዝግጅት ታሪክን ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ከማገዙም በላይ ኢትዮጵያ እና እስራኤል መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የማጠናከር ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡ ወደ ፊት የሚኖሩ መሰል ኩነቶችን በደማቅ መልኩ በጋራ በማዘጋጀት፣ አኩሪ ባህላችንና ታሪካችንን በማስተዋወቅ በራሱ የሚኮራ ትውልድ ለመፍጠር ኢምባሲው ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡በእስራኤል የኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበር ሰብሳቢ Dr. Rose Braun እንዲሁም የቤተ-እስራኤላውያን ተወካዮች በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር ፌስቲቫሉ የኢትዮጵያ እና የቤተ-እስራኤላውያንን ትስስር እና አኩሪ ባህል ለማስተዋወቅ ታልሞ የተዘጋጅ መሆኑን እና ወደፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ላይ ቤተ-እስራኤላውያን ኢትዮጵያ በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን አኗኗር፣ ወደ እስራኤል ሲመለሱ ያጋጠሟቸውን ውጣ ውረዶች እና ኢትዮጵያ ከነበሩ ዘመዶቻቸው ጋር የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች የሚያመለክቱ ፎቶግራፎች እና ግለ-ታሪኮች አቅርበዋል፡፡