ታህሳስ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. በቴል-አቪቭ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኢምባሲ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተካሄደ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ላይ የሚሲዮኑ ባልደረቦች ለግድቡ ግንባታ የሚውል ከአስር ሺህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
በዚህ ወቅት ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ የህዳሴው ግድብ ከተጀምረ ወዲህ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለግድቡ ግንባታ ስኬት የገንዘብ እና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን፣ ግድቡን በሚመለከት በዲፕሎማሲው እና በግንባታው እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ በዝርዝር በማብራራት ግድቡ በአሁኑ ወቅት 94 በመቶ መድረሱ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሚሲዮኑ ባልደረቦች ለግድቡ ግንባታ በዲፕሎማሲው መስክ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ጎን ለጎን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ለሌላው ተምሳሌት መሆን እንደሚገባቸው አክለው አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሁሉም የኢምባሲው ሰራተኞች አገራዊ ደህንነታችንን እና ብሔራዊ ጥቅሞቻችን ለማስከበር እንዲቻል በፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና ዲጅታል ንቅናቄ ስራዎች በንቃት መሳተፍ አስላጊነት ላይ በስፋት ውይይት በማድረግ የተጀመረውን ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠል እንዲቻል መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡