በቴል-አቪቭ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኢምባሲ በአገራችን የልማት፣የገጽታ ግንባታ እና የአድቮኬሲ ስራ አስተዋፅኦ ላበረከቱት ኢትዮጵያውያን እና ቤተ-እስራኤላውያን የምስጋና እና የእውቅና መርሀ ግብር ትናንት ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ተካሄደ።
ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ የምስጋናና የእውቅና መርሀ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር በእስራኤል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ቤተ-እስራኤላውያን በአገራችን የልማት እና ገጽታ ግንባታ ስራ ከፍተኛ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ከዚህ አኳያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ 1.1 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በቦንድ ግዥና በስጦታ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስረድተዋል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅትም ከ49 ሺ የአሜሪካ ዶላር በላይ ድጋፍ መደረጉን እንዲሁም የአገራችንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማስከበር 53,890 የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ መሰጠቱን ጠቅሰው በአጠቃላይ ለተለያዩ የልማት እና የአገር ሉዓላዊነት ማስከበር ስራዎች እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ 1.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር፣ 4.3 ሚሊዮን ብር እና 110,000 የእስራኤል ሼቅል ድጋፍ መደረጉን በአድናቆት ገልጸዋል።
በገጽታ ግንባታ ረገድም የአገራችንን ባህላዊ ምግብ፣ የምግብ ማብሰያ እና መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ባህላዊ አልባሳት፣ ጭፈራ እና የመሳሰሉትን በእስራኤል ማህበረሰብ ዘንድ እንዲታወቅ የጎላ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን አንስተዋል። በአድቮኬሲ መስክም “ስለኢትዮጵያ ዝም አንልም!”፣ “በቃ!”/#Nomore” የመሳሰሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ በአገራችን ላይ የሚደረገውን ያልተገባ ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመቃወም ተንቀሳቅሰዋል ብለዋል። በንግድ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ዘርፎች እንደዚሁ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ቢሆንም ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን አሳስበዋል።
ከዚህ አኳያ የዕለቱ መርሀ ግብር ዋና ዓላማ በእስራኤል ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እና ቤተ-እስራኤላውያን ምስጋና ለማቅረብ እና እውቅና ለመስጠት መሆኑን ገልጸው ወደፊት በአገራችን በሚካሄዱ የልማት፣ የገጽታ ግንባታ እና የአድቮኬሲ ስራ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመጨረሻም የላቀ ተሳትፎ ላደረጉ ማህበራት እና ስብስቦች የእውቅናና የምስጋና ምስክር ወረቀት ተሰጥቶ የመርሀ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram