በእስራኤል የኢትዮጵያ ቀን ዛሬ ሕዳር 30 ቀን 2015 ዓ.ም “ሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለዘላቂ ሠላም” በሚለው መሪ ቃል ተከብሯል። በበዓሉ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የቤተ-እስራኤላዊያን ማሕበረሰብ አባላት፣ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግብ ቤት ባለቤቶች፣ የባህላዊ ልብስ አቅራቢዎች፣ የዕደ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የስፖርት ቡድን አባላት ተገኝተዋል።
በመርሃ-ግብሩ ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔ፣ የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት ከመሆኗም በላይ፣ በብዙዎች ዘንድ ተደናቂነት ያለው ባሕል ያላት በመሆኗ፣ ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን በማጉላትና የሀገር ፍቅርን ለማጎልበት ይህ በዓል ትልቅ ፋይዳ አለው” ብለዋል። በማከልም ይህ ዝግጅት የዳያስፖራ አባላት በአገር ገጽታ ግንባታ የልማት እንቅስቃሴ የበኩላችውን ድርሻ እንዲወጡ ለማስቻል መነሳሳት እንደሚፈጥር ጠቁመው፣ “ኢትዮጵያዊነት ስናከብረው የሚከበር፣ በማንነታችን ውስጥ የሚታይ ውብ እሴት ነው” በማለት ይህ ለዘመናት ያዳበርነው እሴት ተጠብቆ ለአዲሱ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግና ማስቀጠል እንደሚገባ በማሳሰብ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህ ዝግጅት ባሕላዊ ምግብና መጠጥ፣ የአገራችን ቡና፣ የባሕል ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ የባሕል ልብስ እይታ በቆነጃጂቶች መቅረቡ ለበዓሉ ድምቀት ሰጥቷታል።
በማጠቃለያው አስተያየት የሰጡ የበዓሉ ታዳሚዎች የሕዝባችን ጥንታዊ ሥልጣኔና የጥበብ መገለጫ ከሆኑት መካከል አንዱ ባሕላችን በመሆኑ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን በተለይ ወጣቶች ባህላዊ አለባባስና የአመጋገብ ሥርዓታችን እንዲሁም የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን በማቅረብ በማስተዋወቅ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው ገልጸዋል ። በማያያዝም ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና እድገት እንቅፋት የሆኑ፣ አገራችን ለማፍረስ፣ አንድነቷን ለማናወጥ የሚንቀሳቀሱ የጥፋት ኃይሎች ለመከላከልና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትን ለማስከበር ሁሉም በአገር ፍቅር ስሜት በአንድነት እና በሕብረት የመቆም ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል።
 
AmharicEnglishHebrew

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram