በእስራኤል የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ የእስራኤል -አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት (Israeli-Africa Chamber of Commerce) ፕሬዚዳንት ከሚስተር ኒሶ በዝለል (Niso Bezalel)፣ ከንግድ ምክር ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያላ ዊትነር እና የንግድ ምክር ቤቱ አመራር አባላት ጋር በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ምክክር አድርገዋል።

በዚህ ወቅት የእስራኤል አፍሪካ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሚስተር ኒሶ ለክቡር አምባሳደር ተስፋዬ እንኳን ወደ እስራኤል አገር በደህና መጡ በማለት ከእሳቸው ጋር ለመሥራት ያላቸውን ዝግጁነት አሳይተዋል። ሚስተር ኒሶ አያይዘውም ኢትዮጵያ እና እስራኤል ጠንካራ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው መሆኑን እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል በርካታ የኢንቨስትመንትና የንግድ ግንኙነት መኖሩን አስታውሰው ያለውን የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ንግድ ምክር ቤቱ እና በሥሩ ያሉ ከ300 በላይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የቢዝነስ አማራጮች ለመሠማራት ያላቸውን ፍላጎት ገልፀዋል።

አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በበኩላቸው በምክር ቤቱ አመራሮችና አባላት ስለተደረገላቸው አቀባበል ምስጋና አቅርበው፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት በርካታ የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎችን ሲወስድ መቆየቱን እንዲሁም በአገራችን ያሉ ዋና ዋና የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም ዘርፍ እድሎችን በሚመለከት ማብራሪያ ሰጥተዋል። አያይዘውም በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ከታሪካዊ ግንኙነታቸው፣ ከመልክዓ ምድር ቅርበታቸው በተለይም አገራችን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ግብርናን ለማዘመን ያለውን ፍላጎት በመጥቀስ፤ በእስራኤል አገር ካለው የቴክኖሎጂ አንጻር ሲታይ የኢኮኖሚ ትብብሩን ለማስፋት ብዙ መስራት የሚቻል መሆኑን ጠቁመው በእስራኤል የሚገኙ ኩባንያዎች በአገራችን እንዲሰማሩ የንግድ ምክር ቤቱ ከኢምባሲያችን ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት አጠናክሮ እንዲቀጥል በመጠየቅ የኢትዮጵያ መንግስት በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጉ ዘርፎች ትስስሩን የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት በአጽንኦት ገልጸዋል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram