የ”ገበታ ለትውልድ” ፕሮጀክት የገቢ ማሰባሰብ እንዲሁም አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የምስጋና መርሃ-ግብር በክቡር አምባሳደር መኖሪያ ቤት ተካሄደ፡፡በመርሃ-ግብሩ ላይ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ባደረጉት ንግግር አገራችን የበርካታ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም፤ በአግባቡ ባለመልማታቻው የተነሳ ለአገር የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም ሳይሰጡ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት ለቱሪዝም ሴክተር በሰጠው ልዩ ትኩረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች በ”ገበታ ለሸገር”፣ ”ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክት ይፋ በማድረግ ለነዋሪዎች የማይመቹ እና ለጎብኝዎች አሰልቺ የነበሩ ስፍራዎች ተውበው ለቱሪስቶች መስህብ ከመሆናቸው ባሻገር ለበርካታ ዜጎች የስራ እድል እንደፈጠሩ አስገንዝበዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በመልማት ላይ የሚገኙ እንደ ጎርጎራ፣ ኮይሻ፣ ሐለላ ኬላ እና ወንጪ ያሉ ለዓይን ማራኪ እና በርካታ ቱሪስቶች መሳብ የሚችሉ ሆነው እየተገነቡ እንዳለ ጠቅሰው፤ እነዚህን ፕሮጀክቶች እና አዳዲስ በዕቅድ የተያዙ ፕሮጀክቶች ዳር ለማድረስ ሁሉም አገር ወዳድ ወገኖች መረባረብ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ በእስራኤል የሚኖሩ የቤተ-እስራኤላውን ማህበረሰብ፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ለዚህ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በመጨረሻም ጥሪውን አክብረው ድጋፍ ላበረከቱ አካላት የምስጋና የምስክር ወረቀት በመስጠት የዕለቱ መርሀ-ግብር ተጠናቋል፡፡