በቴል-አቪቭ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የ2017 ዓ.ም. አዲስ ዓመት (እንቁጣጣሽ) በዓል ጳጉሜ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. በቴል-አቪቭ በኢምባሲ ጽ/ቤት ጥሪ የተደረገላቸው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልድ ኢትዮጵያውያንና የሚሲዮኑ ባልደረቦች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
በአከባበር ስነ-ስርዓቱ ላይ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ባስተላለፉት የ”እንኳን አደረሳችሁ” መልዕክት በ2016 በአገራችን የተከናወኑ ዋና ዋና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን አብራርተዋል። በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ከመፍጠር አኳያ የብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በይፋ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል። በበጀት ዓመቱ የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በተደረገ ጥረት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዘገብ መቻሉን በመግለጽ ያሉብንን የማክሮ ኢኮኖሚ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ የፖሊሲ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጨምረው አብራርተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሲቪል ግንባታ የማጠናቀቂያ ስራ እየተከናወነ መሆኑን፣ አምስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በዚህ ክረምት በማከናወን እንዲሁም ተጨማሪ ተርባይኖችን በመግጠም የግድቡ ኃይል የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ መድረሱን ገልጸዋል። በዲፕሎማሲው መስክ አገራችን የBRICS ስብስብ አባል መሆኗ ብሄራዊ ጥቅሟን ለመስጠበቅ ተጨማሪ ዓለም አቀፍ መድረክ የተቀላቀለችበት ስኬታማ ዓመት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ አገራችን የባህር በር እንዲኖራት ለማስቻል በቅርቡ ከሶማሌላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን፣ ስምምነቱ በሰጥቶ መቀበል መርህ መሰረት መሆኑን ገልጸው የሶማሊያ ፌዴራል መንግስት የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በመቃወም አሉታዊ የሆነ እንቅስቃሴ እና የአገራችንን በጎ ገጽታ የሚያጎድፍ ተቀባይነት የሌለው ፕሮፖጋንዳ ዘመቻ እያካሄ መሆኑንም አጽንዖት ሰጥተው አስረድተዋል። በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለውን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።