የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/የአፍሪካ ሕብረት የተመሠረተበት 60ኛ ዓመት በእስራኤል ከሚገኙ የተለያዩ የአፍሪካ ኢምባሲዎች ጋር በመተባበር በርካታ ታዳሚዎች በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህ ክብረ በዓሉ ላይ ተቀማጭነታቸው በእስራኤል ያደረጉ የአፍሪካ አገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች፣ የእስራኤል የሠራተኛ ሚኒስትር፣ የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በእስራኤል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ እንግዶች እንዲሁም የተለያዩ የቢዝነስ አካላት እና ታላላቅ ኩባንያ አመራሮች ተሳትፈዋል።
በዚህ ዝግጅት ክቡር አምባሳደር ተስፋዩ ይታይህ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ከሌሎች የአፍሪካ አምባሳደሮች ጋር በመሆን ታዳሚዎች እንኳን ለአፍሪካ ቀን አደረሳችሁ በማለት አቀባበል አድርገዋል። አምባሳደር ተስፋዩ በእስራኤል IETV ከተባለው የተሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ “የአፍሪካ ቀን” ያለውን ትርጉም በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በአፍሪካ ህብረት ምስረታ ላይ የመሪነት ሚና እንደነበራት አስታወሰው አሁንም ለህብረቱ ግቦች መሳካት ለምታደርገው አስተዋጽኦ በሚመለከት ገለፃ አድርገዋል።
በዕለቱ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት የየራሳቸውን የባሕል ምግብ እና ሙዚቃ ትርኢት ለታዳሚዎች አቅርበዋል። በኤምባሲያችን በኩል የአገራችንን ባሕላዊ ምግብ፣ ሙዚቃ እና የአገራችንን መልካም ገፅታ የሚያንፀባርቁ የተለያዩ ምስሎች ለእይታ ቀርበዋል።
በእስራኤል የአፍሪካ አምባሳደሮች ቡድን ዲን እና የእለቱ የክብር እንግዳ የእስራኤል የሠራተኛ ሚኒስትር በዓሉን በማስመልከት ንግግር አድርገዋል።