ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በእስራኤል ፓርላማ (ክኔሴት) አባል ከሆኑት አቶ ሞሼ ሰለሞን ጋር ሐምሌ 11 ቀን 2015 ዓ.ም በፓርላማው ጽ/ቤት በመገኘት ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ወቅት ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ኢትዮጵያ እና እስራኤል ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ሁለቱ አገራት በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በግብርና፣ ትምህርት መስኮች በትብብር እየሰሩ እንደሆነ እና ይኸን ወደ ኢንቨስትመንት፣ የፓርላማዎች ጉድኝት፣ ንግድ እና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትብብር ማስፋት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
አቶ ሞሼ ሰለሞን በበኩላቸው ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ በገለጿቸው መስኮች ትብብሩን የበለጠ ለማጠናከር የኢትዮጵያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በእስራኤል ክኔሴት መካከል የፓርላማ ወዳጅነት መመስረት እንደሚያስፈልግ እና የጽ/ቤታቸው ዋና ኃላፊነት ከአቻ ተቋማት ጋር ወዳጅነቱን መመስረት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የቢዝነስ ትስስርን ከማጎልበት አንጻር በርከት ያሉ ቤተ-እስራኤላውያን ወጣቶች መኖራቸው ራሱ እድል መሆኑን፣ ስለኢትዮጵያ ለማወቅ እና በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ እንዲሁም እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝምን ለማሳደግ በጋራ ለመስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት ተደርጓል፡፡ ክቡር አምባሳደር እና አቶ ሞሼ ሰለሞን በኢትዮጵያ አሁን እየተተገበረ ስለሚገኘው የፕሪቶሪያ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት፣ በጦርነት ወቅት የተጎዱ አከባቢዎች ላይ እየተሰሩ ስላሉት የመልሶ ግንባታ ስራዎች እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ሁኔታዎች አንስተው የተወያዩ ሲሆን የፓርላማ ወዳጅነት መመስረትን በሚመለከት ኢምባሲው ወደ ዋና መ/ቤት በደብዳቤ እንደሚያሳውቅ እና ቀጣይ ኢምባሲውና አቶ ሞሼ ሰለሞን በቅርበት ለመስራት በመግባባት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡