ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በእስራኤል አገር ከሚገኙ ከተለያዩ ማህበራትና አደረጃጀቶች የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሁም ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ኢትዮጵውያንና ቤተ-እስራኤላውያን ጋር በወቅታዊ የአገራችንና አካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መጋቢት 13 ቀን 2016 ዓ.ም በኤምባሲው ጽ/ቤት ውይይት አካሂደዋል፡፡
በወቅቱም ከቡር አምባሳደር ተስፋዬ በፌዴራል መንግስትና በህወሃት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት አተገባበር በጥሩ ደረጃ ላይ መሆኑን፣ በአማራ ክልል ያለው የጸጥታ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት በሚደረገው የህዝብ ውይይት እየተሸሻለ መምጣቱን ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከኦነግ ሸኔ ጋር በመንግስት በኩል ሁለት ጊዜ ታንዛንያ ላይ ለመደራደር ጥረት መደረጉን ሆኖም ግን ኦነግ ሸኔ ባቀረባቸው በድርድር መርህ ተቀባይነት የሌላቸው የመደራደሪያ ሃሳቦች ምክንያት እንዳልተሳካ ገልጸዋል፡፡ በመንግስት በኩል ወደፊትም ለህዝቡ ሰላም ሲባል ለመደራደር ቁርጠኛ መሆኑን እንዲሁም በቅርቡ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት አስመልክቶ ክቡር አምባሳደር ገለጻ አድርገዋል፡፡ በተሳታፊዎቹ በኩል በኢትዮጵያ ሰላም፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በተለይም የህዝብ ለህዘብ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች የበለጠ ከማጠናከር አኳያ እነርሱ ሊጫወቱት ስለሚገባ ሚና እና ተያያዥ አስተያየትና ጥያቄዎች አንስተው በክቡር አምባሳደር ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በቀጣይም በየወቅቱ እየተገናኙ ለመወያየት እና ስራዎችን በመቀራረብ ለመስራት መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡