በቴል-አቪቭ የኢትዮጵያ ኢምባሲ 128ኛው የአድዋ ድል መታሰቢያ ቀን “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል የካቲት 21 ቀን 2016 ዓ.ም. በቴል-አቪቭ ሬይኔሳንስ ሆቴል አክብሯል፡፡
በአከባበር ስነ-ስርዓቱ ላይ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ ባሰሙት የመክፈቻ መልዕክት በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የሚመራው የኢትዮጵያ ጦር በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስ የሰለጠነውን፣ ዘመናዊ ጦር መስሪያ የታጠቀውንና በአግባቡ የተደራጀውን የኢጣሊያ ጦር አድዋ ከተማ አቅራቢያ ገጥሞ አንፀባራቂ ድል እና የጦርነቱን ዋና መንስኤ የሆነውን የውጫሌ ስምምነት አብራርተዋል፡፡ አድዋ ድል፣ ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘ እና አርበኝነት፣ አንድነት እና የእናት አገር ፍቅር የሚያላብስ ድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአድዋ ድል የኢትዮጵያን ነፃነትና ሉዓላዊነት ከማስከበሩም ባሻገር በጥቁር ህዝቦች ዘንድ የፀረ-ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄ እንዲቀጣጠል ተምሳሌት የሆነ ታሪካዊ ድል መሆኑን ያብራሩት ክቡር አምባሳደር ከዚህም አኳያ በዘንድሮ ዓመት የአድዋን ድል የሚመጥን የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም በአዲስ አበባ ተመርቆ ለጎኝዎች ክፍት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛዋ ለቅኝ ግዛት እጇን ያልሰጠች አገር መሆኗን የገለጹት ክቡር አምባሳደር ባላት ረጅም ታሪኳ ውስጥ የማንንም አገር ግዛት ለመውረር የሞከረችበት አጋጣሚ እንደሌለ ይልቁንም ለፓን አፍሪካኒዝም ፍልስፍና እውን መሆንና በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምትጫወተው ሚና ገልጸዋል፡፡ ክቡር አምባሳደር ተስፋዬ አያይዘውም የኢትዮጵያ እና አከባቢዋን በሚመለከት ያሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እንዲሁም በኢትዮጵያና እስራኤል መካከል ያለውን ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በበዓሉ አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ Col.David ben Tarzan የተባሉ፣ በኢትዮጵያ በርካታ ስፍራዎችን የጎበኙ የኢትዮጵያ ወዳጅ ስለአድዋ ድል ገለጻ አቅርበዋል፡፡ በገለጻቸውም እ.ኤ.አ 1890ዎቹ ፋሽስት ወራሪ በሰለጠነ ወታደራዊና የመሳሪያ ዝግጅት አድርጎ በኤርትራ በኩል አድርጎ ወደ አድዋ አከባቢ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ከ17 ሺ በላይ ሰራዊት የያዘ ወራሪ አድዋ ሰፍሮ ሳለ አፄ ምኒልክ ባደረጉት የክተት ጥሪ መሰረት የኢትዮጵያ ጀግኖች በደቡብ አቅጣጫ ከበባ በማድረግ፣ የጣሊያንን ኃይል በመከፋፈል በማይታመን ሁኔታ በማጥቃት ድል እንደተቀዳጁ የቦታዎቹን ምስል በማቅረብ ስለአድዋ ድል ታላቅነት አስረድተዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከእስራኤል ውጭ ጉዳይ፣ ከመከላከያ እና ሌሎች ተቋማት ኃላፊዎች፣የአፍሪካ አምባሳደሮች፣የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ኢትዮጵያውያንና ቤተ-እስራኤላውን፣የሚዲያ ባለሙያዎች እና የሚሲዮኑ ባልደረቦች ተሳትፈዋል፡፡
 

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram