ኢምባሲያችን በእስራኤልና በኢትዮጵያ መካከል የቅባት እህሎች ንግድ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም አገራችን በእስራኤል ያለውን የሰሊጥ ገበያ እድል የበለጠ ለማስፋት በሚደረገው እንቅስቃሴ የንግድ ምክክር በዛሬው ዕለት ያካሄደ ሲሆን፤ ከኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመሞች አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበር ጋር በመተባበር የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት መርሃግብር አዘጋጅቷል።

በኢምባሲያችን በተዘጋጀው መድረክ በማህበሩ የሥራ ኃላፊዎች የተመራ 28 አባላት ያሉበት የቢዝነስ ልዑካን የተሳተፉ ሲሆን ከእስራኤል የሰሊጥ ገዥ ድርጅቶችና ባለሃብቶች ጋር የአቻ ለአቻ የንግድ ምክክር ተደርጓል። በዚህ መድረክ መክፈቻ ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ ባደረጉት ንግግር በአገራችን የወጪ ንግድ ለማስፋፋት የሚከናወኑ ተግባራት፣ የአገር ውስጥ ምርቶችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ በመንግስታችን ለምርት ጥራት ልዩ ትኩረት የተሰጠ መሆኑን፣ በተጨማሪም እስራኤል የአገራችንን ሰሊጥ ከሚገዙ አገሮች ቀዳሚ በመሆኗ፣ ከአገሪቱ ጋር ያለንን የገበያ እድል ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘርፉ የተሠማሩት ላኪዎች በእስራኤል ጉብኝት ማድረጋቸው የሁለትዮሽ ንግድ ግንኙነት ለማጠናከር ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎች እና ቅመማቅመሞች አዘጋጅቶ ላኪዎች ማሕበር የቦርድ አባል አቶ ሳሙኤል መልኬ በአገራችን በቅባት እህሎች ንግድ ያለውን አቅም፣ የወጪ ንግድ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለመሆን በጥራትና በብዛት ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት ጠቅሰው፣ የአገራችን የቅባት እህል ገበያ ተደራሽነት እና አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት በአሃዝ የተደገፈ መረጃ አቅርበዋል፤ በዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስራኤል የሚገኙ ነጋዴዎች የአገራችንን ሰሊጥ በመግዛት የንግድ ትስስሩ እንዲጠነክር ጉልህ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን አስረድተዋል።

በመድረኩ የአገራችንን ሠሊጥ ከሚያስመጡ የእስራኤል ባለሃብቶችና ኩባንያዎች ጋር አጠቃለይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ በኩባንያዎቹ በኩል ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት የተሻለ የቅባት እህል ያላት መሆኑንና ከአገራችን ጋር ያላቸውን የንግድ ግንኙነት ማሳደግ እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል፣ ሆኖም ለንግድ ሥራው እንቅፋት ከሆኑት ችግሮችን መካከል የጥራት ችግር፣ በታዘዘው ወቅት አለማድረስ፣ የመጓጓዣና የግዥ ሥርዓት አለመዘመን በሚመለከት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎች በክቡር አምባሳደር ረታ እና በማሕበሩ ተወካዮች ምላሽ ተሰጥቷባቸዋል።

ልዑካን ቡድኑ በነገው እለት በዓለምአቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ የእስራኤል የሰሊጥ ምርቶች አቀነባባሪ ፋብሪካዎችን በመጎብኘት ስለ ንግድ ልውውጠ ምክክር ያደርጋሉ።

AmharicEnglishHebrew

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram