በእስራኤል የኢትዮጵያ ኢምባሲ አዘጋጅነት የኢትዮጵያን የዘመን መለወጫ (የ2015 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት) ዋዜማ “አንድነታችን በዘመናት አብሮነታችን የተገነባ እሴታችን ነው”!! በሚለው መሪ ቃል ዛሬ ጳጉሜ 04 ቀን 2014 ዓ.ም. በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል። በዚህ መድረክ የአፍሪካ አምባሳደሮች፣ የእስራኤል የመንግስት አካላት፣ ታዋቂ ምሁራንና የቢዝነስ አካላት፣ ጋዜጠኞች፣ በርካታ የቤተ-እስራኤል ማህበረሰብ አባላት፣ ኢትዮጵያዊያን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳትፈዋል።
መርሃ-ግብሩ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር የተጀመረ ሲሆን፤ በመርሃ-ግብሩ መክፈቻ ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ በእስራኤል የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር እና ልዩ መልዕክተኛ እንቁጣጣሽ! እንኳን ለኢትዮጵያ 2015 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል አደረሰን! አደረሳችሁ! በማለት ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ የጥንታዊ ታሪክና የጥበብ ባለቤት፣ የነጻነት ፋና ወጊ እና ለጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነች በተፈጥሮ ሃብት የታደለች፣ ታላቅ ሀገር ናት። የዘመን መለወጫ በዓል ስናከብር ያለፈውን ጊዜ እያስታወስን፣ አሁኑና መጭውን የምናስብበት፣ ያለፈው ጊዜ ሁሌም ታሪክ ነው። ታሪክ ለሕዝብ ትልቅ ሃብት ነው። ይህን ሀብት ለመልካም ስንጠቀምበት ለአሁኑ ማንነታችን፣ አንድነታችን ስኬታችን መሰረት፣ ለነገ ራዕይን ለመሰነቅ መነሻችንም ነው። ስለሆነም ዘመንን ስናከብር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን አስተሳስረን እያስብን ነው። ኢትዮጵያ ልዩ ከሚያደርጓት ነገሮች አንዱ የራሷ የሆነ ጥንታዊ የዘመን አቆጣጠር ባህልና እሴት ያላት አገር መሆኗ ነው” በማለት ክቡር አምባሳደር ረታ ይህን እሴታችን ጠብቀን ለማስቀጠልና ለሌላው ዓለም ለማሳወቅም የዘመን መለወጫ በዓላችንን ሥርዓቱን ጠብቀን እያከበርን እንገኛለን ብለዋል።
በአገራችን ደረጃ የጳጉሜ ቀናት በልዩ ሁኔታ ማለትም የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን፣ የአምራችነትን፣ የሰላምና አንድነት ቀን በማክበር ሰንብተናል። እየተከበሩም ይገኛሉ። እነዚህን ቀናት ስናስብና ስናከብር በአገራችን የነበሩ ፈተናዎችን እና ተግዳሮቶችን አልፈን በቀጣይም ጉዟችን ስኬታማ እንዲሆን መልካም እድሎችንና ብሩህ ተስፋን ሰንቀን ነው ብለዋል። በመቀጠልም ባለፈው ዓመት ብዙ ተግዳሮቶች የገጠሙን ቢሆንም እነዚህን ለአገራችን ሕልውና የነበሩ ፈተናዎችን አልፈን በአገራችን በህዝቧ የጸና አንድነትና ተስፋ ትልልቅ ሁነቶችንና ክንውኖችን፣ ጠቃሚ ክስተቶች የተካሄዱበት ዓመት እንደነበር ተናግረዋል። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ውሃ ሙሌት እና ሁለተኛ ተርባይን ኃይል ማመንጨት መጀመሩን፣ በአረንጓዴ አሻራ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዛፎች መተከላቸውን በማስታወስ፤ በእስራኤል የሚኖረው የዳያስፖራ አባላት እና የአገራችን ወዳጆች ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ስራዎችን በመደገፍ ለሚያደርጉት አስተዋፆኦ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀጣይ ከውጭም ሆነ ከውስጥ በአገራችን ላይ በሚቃጣው ጫናና የሀሰተኛ ዘገባዎች በመከላከል ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን በመቆም አገራችንን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ክቡር አምባሳደር “መጪው አዲስ ዓመት በአገር ውስጥ ሆነ በውጭ አገር ያሉ ወገኖች አንድ ላይ በመሆን የጥፋት ኃይሎች አገራችን ለማፍረስ፣ አንድነቷን ለማናወጥ የሚንቀሳቀሱትን የምናሳፍርበት ጸንተን ለአንድነታችን የምንዋጋበትና የምንቆም መሆኑን የምናስመሰክርበት ወቅት ነው” ብለዋል። ስለሆነም ኢዲስ ዓመትን ስናከበር የዘመኑ ትውልድ የአገራችንን አንድነቷንና ነጻነቷን ከማስከበርም በተጨማሪ የታፈረች፣ የበለጸገች፣ ታላቅና የተከበረች ሀገር ለመጭው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።
የበዓሉ ታዳሚዎች “ኢትዮጵያዊነት የአንድነት እና የነጻነት መገለጫ ነው” የአገራችን አንድነት ለማስከበር ቃል-ኪዳን እንገባለን በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። በማጠቃለያው ሁሉም ተሳታፊዎች ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና እድገት የድርሻቸውም ለማበርከት ቃል-ኪዳን ገብተዋል። በእለቱ የአገራችን ቡና፣ ባሕላዊ ምግብና መጠጥ እንዲሁም የባሕል ዘፈኖችና ውዝዋዜዎች ለታዳሚዮች በመቅረቡ መርሃ-ግብሩን ከማድመቁ ባሻገር፤ አገራዊ ድባብ ሰጥቶታል።

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram