ኢምባሲያችን የእስራኤል የግብርና ቴክኖሎጂ እና አዳዲስ አሰራሮችን ወደ አገራችን ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት መልህቅ ኩባንያዎችን በመለየት ከአገራችን የግብርና ሚኒስቴር የአመራር አካላት እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ጋር በበይነ-መረብ ውይይት አካሂዷል። በመድረኩ በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፣ የአገራችን የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ የእስራኤል ባለሃብቶች እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፤የኩባንያዎች ተወካዮች በአገራችን ለመሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ገለጻ አቅርበዋል።

በውይይቱ መጀመሪያ በእስራኤል የተሻለ የግብርና ምርትና አሠራር ውጤቶች ላይ የሚያተኩር Bio Feed የተባለ ኩባንያ ማኔጅንግ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ኑምሩድ እስራኤሊ ዘላቂ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማምጣት የሚያስችል Dream Value የተባለ በተለያዩ አገራት አዋጪነቱን ያረጋገጡበትና ለትርፋማነቱ የሚተማመኑበት የቢዝነስ ሞዴል በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል። ዶ/ር ኑምሩድ አክለውም አሁን ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ለኢኮኖሚ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት እና ቁርጠኝነት እንዲሁም ምቹ የአካባቢ ሁኔታ በመመልከታቸው፣ ይህንን ሞዴል በኢትዮጵያ ተግባራዊ ቢደረግ ገበሬዎች ምርታቸውን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ውጤት የሚያስገኝ መሆኑን አሳውቀዋል። በመቀጠል በእስራኤል የዓለምአቀፍ የልማት ትብብር ኤጄንሲ (ማሻቭ) የመንግስትና የግል ሽርክና (PPP) ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ሚ/ር ሻሎም ትርጉማን በ”ማሻቭ” ፕሮጀክት የመንግስትና የግል በሽርክና ሞዴል አማራጭ የፕሮጀክት ሀሳብ በሚመለከት ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፤ በተለይ የግብርና ልማት በአተክልትና ፍራፍሬ ልማት ትብብር ለማድረግ ያለውን አቅም አስረድተዋል። በመጨረሻም በአገራችን በስንዴ እርሻ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት በሂደት ላይ የሚገኘው የሜትሬሊ ኩባንያ ተወካይ ሚ/ር ሮይ በበኩላቸው ኩባንያው ያለውን አቅም፣ በዘርፉ የሚደረገውን እንቅስቃሴ፣ በአገራችን ኢንቨስት ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ጥረትና ጉዳዩ የደረሰበትን ሁኔታ በሚመለከት ገለጻ አቅርበዋል።
በመድረኩ ተሳትፎ ያደረጉት የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ አመራሮች ለተደረገው ገለጻ ምስጋና በማቅረብ፤ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ካለው ወዳጅነት አንፃር ሚኒስቴር መ/ቤቱ የግብርና ዘርፍን ለማዘመን ከያዘው ዕቅድ አንጻር ከኩባንያዎች ጋር በትብብር የመስራትን አስፈላጊነት በመግለጽ፤ ፕሮጀክቶቹ በአገራችን ተግባራዊ እንዲሆኑ ከየዘርፎቹ ቡድን ጋር በመተባበር ያላሰለሰ ጥረት እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። አክለውም የተለያዩ ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎች ባለሃብቶቹ ምላሽ ሰጥተዋል።
በኢምባሲያችን በኩል የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት ክቡር አምባሳደር ረታ ዓለሙ የአገራችን የግብርና ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ በእስራኤል ከፍተኛ አቅም እና ፍላጎት የሚያሳዩ ትላልቅ ኩባንያዎች በመኖራቸው፣ የአገራችን የግብርና ዘርፍ በቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ሀሳብ ያቀረቡት ድርጅቶች የሥራ ጉብኝት እንዲያደርጉ ሁኔታዎች የሚመቻች መሆኑን አስታውቀዋል። በማያያዝም እነዚህ ኩባንያዎችን ወደ ሥራ ማስገባት ለአገራችን የሚኖረውን ፋይዳ በማብራራት፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመረባረብ አገራችንን ከውጭ በሚገኙ የቴክኖሎጂ ድጋፎች ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚስፈልግ፤ ለዚህም ኢምባሲያችን የተጠናከረ ጥረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

AmharicEnglishHebrew

Disclaimer: The official text of the Embassy Website is the English language version. Any discrepancies or differences created in translations are not binding and have no legal effect for compliance or enforcement purposes.

X
Twitter
Facebook
YouTube
Instagram